የአዳማ ቁ.2 ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤ/ክ

የአዳማ ቁጥር 2 ሙሉ ወንጌል አመሰራረት በቀደመዉ ጊዜ በከተማዉ ዉስጥ የነበረችዉ አንድ የሙሉ ወንጌል አጥቢያ እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ አንድ አጥቢያ የነበረች ሲሆን በከተማ የነበሩትን አራት አቅጣጫዎች አራት አጥቢያዎችን ለመክፈት በወቅቱ በነበሩት መሪዎች ታስቦ በዚሁ መሠረት ቀጠና 1 ፣ ቀጠና 2 ፣ ቀጠና 3 እና ቀጠና 4 በማለት የፀሎት ቤት ጅማሬ ተደረገ፡፡ ከሶስቱ ቦታዎች ቀድሞ ቀጠና 2 ይባል የነበረዉ የአሁኑ ቁጥር 2 ሙሉ ወንጌል መሃል ላይ በመገኘቱ የነበረዉ አንድ አጥቢያ ሁለት ቦታ እንዲከፈል እና አገልጋዮችም በዚሁ መሠረት በሁለቱ ቦታዎች ተደልድለዉ አንድ የነበረችዉ አጥቢያ ሁለት ቦታ ተከፍላ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 ሙሉ ወንጌል በመባል  በ1996 ዓ.ም ታህሳስ ላይ የአጥቢያ ስያሜ  ይዛ ጀመረች፡፡ ከዚህ በፊት በሃሳብ ተጀምረዉ የነበሩትን አጥቢያዎች በየራሳቸዉ ጂኦግራፊያዊ አቅጣጫ በመጠቀም አጥቢያዎችን በመትከል እየሰሩ በአሁኑ ጊዜ 17 አጥቢያዎች የደረሱ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ በቁጥር 2 ሙሉ ወንጌል ሥር አጥቢያ የወጡት ገንደ ጋራ ሙሉ ወንጌል ፣ ሰላም ሰፈር ሙሉ ወንጌል ፣ ገንደ ኦዳ ሙሉ ወንጌል ፣ ኬላ ሙሉ ወንጌል እና ሮጌ ሙሉ ወንጌል ሲሆኑ ሌሎችንም ከከተማ ዉጪ ያሉ አጥቢያዎችንም መስርታለች፡፡

ራዕይ

ሁለንተናዊ አገልግሎት በመስጠት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተለወጡና የተሞሉ ምዕመናንን ማየት፡፡

ተልዕኮ

የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በወንጌል ባልተዳረሱ ቦታዎች በመስበክ አጥቢያ ቤተክርስቲያንን በመትከልና አማኞችን እውነተኛ ደቀመዛሙርት በማድረግ ለሁለንተናዊ አገልግሎት ማዘጋጀት ነው፡፡

ግብ

የዳኑ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉና እውነተኛ ደቀመዝሙር የሆኑ በርካታ ሰዎች ተጨምረው ማየት፡፡