የወጣቶች ፕሮግራም

የወጣቶች ፕሮግራም ለቤተክርስቲያን ትልቅ ትርጉም ያለዉ ሲሆን ይኸዉም ወጣቶች በዓለም ሲስተም እንዳይዋጡ እና በጉብዝና ጊዜያቸዉ ጌታን እንዲያመልኩ እንዲሁም እንዲያገለግሉ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነዉ፡፡ (መክ 12÷1)

ለቤተክርስቲያንም ተተኪ አገልጋዮችን በማፍራትም ረገድ ትልቅ ሚና ያለዉ ፕሮግራም በመሆኑ በልዩ ልዩ ጸጋ (በጸሎት ፣ በዝማሬ ፣ ቃል በማካፈል ፣ በድራማ እና ስነጽሑፍ ) የሚያገለግሉ ወጣቶችን ጌታ እየረዳን በማየት ላይ እንገኛለን፡፡ ክብር ለአምላካችን ይሁን!

የወጣቶች ፕሮግራም በቤተክርስቲያናችን ካሉት ዋና ዋና ፕሮግራሞች አንዱ ሲሆን ፕሮግራሙ የሚካሄደዉ ዘወትር ቅዳሜ ከቀኑ 10፡30 እስከ ማታ 1፡00 ሰዓት ነዉ፡፡

ፕሮግራሞቻችን

  • የጸሎት
  • የዝማሬ
  • የቃል እንዲሁም የስነ-ጽሑፍ ይዘት ያለዉ ሲሆን

በተጨማሪ

  • የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ቀን
  • የአምልኮ ምሽት እና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችንም በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን፡፡

ፕሮግራሞቻችንን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ የTelegram Channel የከፈትን ሲሆን በዚህም ቻናል የዝማሬ ፣ የቃል እና የስነ-ፅሑፍ ፕሮግራሞችን ቅጂ ጌታ በረዳን መጠን እየለቀቅን እንገኛለን፡፡ ከዚህም ቻናል ጎንለጎን የTelegram Group የተከፈተ ሲሆን በዚህም ወጣቶች እርስ በእርስ እንዲገናኙ እና የወደዱትን መዝሙር ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንዲከፋፈሉ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡

የወጣቶች ፕሮግራም የተዘጋጀዉ ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ታዳጊዎችን ጨምሮ ሁሉንም የዕድሜ ክፍል ታሳቢ ያደረገ ነዉ፡፡ ይህም በመሆኑ በታዳጊዎች ዉስጥ ጌታ ያስቀመጠዉን ጸጋ ወጥቶ ወላጆች በማየታቸዉ በጣም ደስተኛ መሆናቸዉን አንዳንድ ወላጆች ገልጸዉልናል፡፡ ታዳጊዎችን እንዲያገለግሉም እያበረታታን እንገኛለን፡፡

ተማሪ የሆኑንትንም ወጣቶች በትምህርታቸዉ ጥሩ ዉጤት እንዲያመጡ እያበረታታን እና የላቀ ዉጤት ያመጡትንም እየሸለምን እንገኛለን፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚሄዱትንም ወጣቶች ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸዉ በፊት ሊያዉቁት የሚገባቸዉን አንዳንድ ነገሮች እንዲያዉቁ አስፈላጊዉን ምክር እንዲያገኙ እንዲሁም በድል እንዲመለሱ የፀሎት ጊዜን  በፕሮግራማችን ዉስጥ አካትተናል፡፡

ይሄንንም የወጣቶች ፕሮግራም አገልግሎት ለማስፋት በአዳማ ከተማ ከሚገኙ የሙሉ ወንጌል አጥቢያዎች ጋር በጋራ እየሰራን እንገኛለን፡፡